Back to List 

ዩኒቲ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ የሊደርሺፕ ዴቨሎፕመንት ፕሮግራም ሠልጣኞቹን አስመረቀ

ዩኒቲ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ የሊደርሺፕ ዴቨሎፕመንት ፕሮግራም ሠልጣኞቹን አስመረቀ




በዩኒቲ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ የሊደርሺፕ ዴቨሎፕመንት ፕሮግራም ክፍል የመጀመሪያው ዙር የመጀመሪያ ሳይክል የሊደርሺፕ ሠልጣኞች የምረቃ ስነስርዓት  ቅዳሜ በ21/11/99 በዩኒቨርሲቲ ኮሌጁ የባህል ማዕከል በድምቀት ተከበረ፡፡


ላለፉት 18 ወራት የሊደርሺፕ ስልጠና ሲከታተሉ የነበሩት 30 ሰልጣኞች በነበራቸው ቆይታ በግላቸው የባህሪ ለውጥ ከማምጣት አንስቶ ግላዊና ሀገራዊ ራዕይን የሰነቀ ማንነትን እስከ ማጎልበት ብሎም ለሌሎችም መልካም ማሰብን ለሥራ ተነሳሽነትን እና በሌሎችም እጅግ ጠቃሚ ጉዳዮች ላይ ሲሰለጥኑ መቆየታቸው ታውቋል፡፡ በዩኒቲ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ የፐሮገራሙ መስራችና አሰልጣኝ ዶ/ር ፍስሐ እሸቱ በምርቃቱ ስነ ሥርዓት ላይ ባስተላለፉት መልዕክት ከዚህ ፕሮግራም ሰልጥኖ መመረቅ ማለት አንድ ሠልጣኝ በህብረተሰቡ ውስጥ ገብቶ አመርቂ ሥራ ሲሠራ ከራሱ አልፎ ለሌላው ወገን ሲተርፍ እና እንዲሁም የህብረተሰቡን ምስክርነት ሲያተርፍ መሆኑን በመግለፅ የዛሬው ዝግጅት ከአንደኛው የጥናት ቆይታ ወደ ሁለተኛው ቆይታ (ሳይክል) በድል ስለመሸጋገራችሁ የምናበስርበት ነው በማለት መልዕክታቸውን አጠናክረዋል፡፡ የምረቃውን ዝግጅት የዩኒቲ ግሩቭ ባንድ በጣፋጭ ዜማዎች የዕለቱን የክብር እንግዶች፣ የተመራቂ ቤተሰቦች እና ሌሎች ተጋባዥ እንግዶችን ስያዝናና በመቆየት የምረቃ በዐሉን አድምቆታል፡፡


በመጨረሻም የመጀመሪያው ዙር የመጀመሪያ ሳይክል ተመራቂዎች ከዕለቱ የክብር እንግዳ ከአምባሳደር ብርሃኑ ዲንቃ እጅ የተሳትፎ የምስክር ወረቀታቸውን ከተቀበሉ በኋላ በአምባሳደሩ አባታዊ፣ ጠቃሚና አበረታች የመዝጊያ ንግግር የዕለቱ ፕሮግራም ፍጻሜ ሆኗል፡፡

Date    2007-11-15 17:49:51