ለዓለም ሰላም መስፈን የእያንዳንዱ ግለሰብ አስተዋጽኦ አስፈላጊ መሆኑ ተገለጸ
በዩኒቲ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ የሊደርሽፕ ደቨለፕመንት ፕሮግራም በዓይነቱ ለየት ያለና በተለያዩ ማህበራዊ ጉዳዮች ላይ ሰፊ ገለፃ የተደረገበት ውይይት ሰኔ 30/1999 ዓ.ም በዩኒቨርሲቲ ኮሌጁ የባህል ማዕከል አዳራሽ አካሄደ፡፡
በዩኒቲ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ የፕሮግራሙ መስራችና መሪ የሆኑት ዶ/ር ፍስሐ እሸቱ በዕለቱ ለተጋበዙት ከሁለት መቶ በላይ ለሚሆኑ ታዳሚዎች ሦስት ሰዓት የፈጀና በወቅቱ የዓለማችን የሰላምና ሌሎችም አንገብባቢ ጉዳዮች ላይ ገለፃና ማብራሪያ ያካተተ ውይይት አድርገዋል፡፡ ዶ/ር ፍስሐ እንደገለጹት በአሁኑ ጊዜ በአለማችን ላይ ላሉት ችግሮች መባባስ ከየአንዳዳችን አስተሳሰብ ጀምሮ በጠቅላላው የአለም ሕዝብ ዘንድ የነገሰው የግለኝነት፣ የእኔ እበልጥ አስተሳሰብ መሆናቸውን ጠቅሰዋል፡፡ በመሆኑም በሰው ልጆች መካከል ያለው ችግር ተወግዶ በአለም ላይ ሰላም የሚሰፍነው እያንዳንዳችን በአእምሮ ብልጠት ብቻ የረሳችንን ፍላጎት ከማሳካት ይልቅ በቅን ልቦናችን የማሰብ ልምዳችን ቢዳብር የእያንዳንዳችን ኑሮ በሰላም እና በእረፍት የተሞላ ከመሆኑም ባሻገር የዚህ ዓይነት አስተሳሰብ መስፋፋት ለአለም ሰላም መስፈን ብቸኛው አማራጭ መሆኑንም ገልፀዋል፡፡
በማስከተልም ለአለም ሕዝቦች መከባበርና መደጋገፍ ብሎም ለአለም ሰላም መስፈን የእያንዳንዳችን አስተዋፅኦ ወሳኝ መሆኑን ከተረዳን እና ሁላችንም የበኩላችንን አስተዋፅኦ ለማበርከት ከተዘጋጀን ከእኛ ከጥቂቶቹ መጀመር ይቻላል በማለት “የብርሃን ማህበረሰብ ኩሩ አባል” በሚል ስያሜ የሚታወቅ “በዕውቀት፣ በሐብት፣ በፆታ፣ በሃይማኖት፣ በዘርና በፖለቲካ ያልተከፋፈለ ማህበረሰብ መመስረቱን ይፋ አድርገዋል፡፡ማንኛችንም ለዚህች ዓለም ሰላም መስፈን የእኔ አስተዋጽኦ ያስፈልጋል ብለን የምናምን ሰዎች ከላይ በተጠቀሱት ልዩነቶች ሳንከፋፈል ለአለም ችግሮች ብርሃን ሆነን መነሳታችንን ለማስመስከር ዛሬ መወሰን ይገባናል፡፡ ሀገራችን የሰው ዘር መገኛ ብቻ ሳትሆን የመልካም ነገር መፍለቂያ እንዲትሆን በተግባር ለመተርጎም በአንድነት አመንን፣ ፀናን ሲሉ በዕለቱ ለታዳሚዎች በታደለው ጽሑፍ ላይ ገልፀው ከዩኒቲ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ማህበረሰብና ከሌሎች ተቋማት ከተጋበዙት ታዳሚዎች መካከል ፈቃደኛ ሆነው ከተመረጡት ሰባት አባላት ያለው ዐብይ ኮሚቴ አቋቁመዋል፡፡
በመጨረሻም ቀጣዩ “የብርሃን ማህበረሰብ ኩሩ አባል” ስብሰባ ሐምሌ 14/1999 ተላልፎ በአእምሮዎ ያሰቡትን መልካምና የራስዎ የሆነውን አዲስ ዓለም ለመፍጠር ወደሚያስችልዎት የብርሃን ማህበረሰብ ይምጡ በሚል ጥሪ የዕለቱ ስብሰባ ፍፃሜ ሆኗል፡፡
Date 2007-07-13 07:10:27